
” አንዳንዶች እነዚህን ምስሎች የቀድሞ የፍቅር አጋራቸውን ለመበቀል ይፈጥራሉ ” – ተመራማሪዎች
ዓለማችን በተለያየ ጊዜ በርከት ያሉ የተራቀቁ ቴክኖሎጂዎችን እያስተናገደች ነው የመጣችው። ከቴክኖሎጂዎቹ ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ ስጋቶችንም በዛው ልክ አስተናግዳለች።
አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) የወቅቱ አነጋጋሪው ቴክኖሎጂ ሲሆን ጥቅሙም ስጋቱም በዛው ልክ እየጨመረ መጥቷል።
በዓለም ላይ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) በመታገዝ የሚፈጠሩ የእርቃን ምስሎች ስጋትነታቸው ከቴክኖሎጂው መዘመን ጋር እየጨመረ መጥቷል።
የአሜሪካ 38 ግዛቶች በዲፕፌክ የሚሰሩ የህፃናት የእርቃን ምስሎች ላይ እገዳ ቢጥሉም የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ዌብሳይቶች የእርቃን ምስሎችን ለመስራት በመቅለላቸው ስጋታቸው አይሏል።
በእነዚህ ዌብሳይቶች ሰዎች የሚያውቋቸውን ሰዎች ምስል በማስገባት ወደ እርቃን ምስልነት እንደሚቀይሩ ተገልጿል። ምስሎቹ ለእውነትነት የቀረቡ በመሆናቸው ሰዎች ለመለየት እንደሚቸገሩ ባለሙያዎች አስረድተዌ።
የኮምፒውተር ሳይንስ ባለሙያው ማይክል ዚመር ፤ ምስሎቹ ፍፁም እውነተኛ እንደሚመስሉና በርከት ያሉ የመተግበሪያ ድርጅቶች እንደዚህ አይነት ምስል የሚሰሩ መተግበሪያዎችን ማስወገዳቸውን ገልጿል።
ይህንን የሚሰሩ ድህረገጾች ግን አሁንም መኖራቸውን ባለሙያው ተናግሯል።
ዚመር ” የፎቶ ኤዲቲንግ ቴክኖሎጂው በጣም ዘምኗል ” ያለ ሲሆን ” አሁን ላይ እነዚህን የእርቃን ምስሎች ለመፍጠር አንድ ክሊክ ብቻ በቂ ነው ” ሲል አብራርቷል።
ኤሊስተን ቤሪ የተባለች የ14 አመት ልጅ በእንደዚህ አይነት መንገድ የእርቃን ምስል እንደተሰራባት ትናገራለች።
ይህንን ምስሏንም ከ2400 የሚበልጡ የትምህርት ቤቷ ተማሪዎች እንደተመለከቱት ገልጻለች።
‘ ቶርን ‘ የተሰኘ ድርጅት ዕድሜያቸው ከ13-20 በሚሆኑ 1200 ልጆች ላይ ጥናት ማድረጉን ገልፆ በጥናቱ ከስምንቱ ልጆች አንዱ በዲፕፌክ በተሰራ የእርቃን ምስል የተጠቃ ሰው እንደሚያውቅ እንደዚሁም ደግሞ ከ17 ሰዎች አንዱ እራሱ የዚህ ድርጊት ሰለባ አንደሆነ መታወቁን ይፋ አድርጓል።
ተመራማሪዎች አንዳንድ ህፃናት እነዚህን ምስሎች ማወቅ ስለሚፈልጉ ብቻ ይፈጥራሉ ያሉ ሲሆን አንዳንዶች የቀድሞ የፍቅር አጋራቸውን ለመበቀል ይፈጥራሉ ብለዋል።
በአሜሪካ በርካታ ግዛቶች ያለ ግለሰቡ ፈቃድ የእርቃን ምስል መፍጠርና ማጋራት ወንጀል ቢሆንም አሁንም ጉዳዩ አስጊነቱ በመጨመሩ ጥንቃቄ ያሻል ተብሏል።
በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) በመታገዝ የሚፈጠሩ ምስሎች እና ቪዲዮዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ውስብስብ እየሆኑ የመጡ ሲሆን እውነተኛ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ስለሚከብድ ነገሩን በጥንቃቄ ማየት ይገባል።
ፎክስ 6 EthioNews #Ethiopia