
” በአንድ ዓመት ብቻ 16 ሕፃናት እና በመቶዎች የሚቆጠሩ ከብቶች በታጣቂ ቡድኑ ተወስደዋል ! “የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ኦጉላ ኡጁሉ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ እንደገለፁት በትናትናው ዕለት ከቀኑ 7 ሰዓት አከባቢ በአኝዋክ ብሔረሰብ ዞን በጎጊ ወረዳ ተዶ በሚጠራዉ አከባቢ የሙርሌ ታጣቂዎች አራት ሴቶችን አፍነዉ መዉሰዳቸዉን ተናግረዋል።” ሙርሌ” የተሰኘዉ የደቡብ ሱዳን ታጣቂ ቡድኑ ከ14 እስከ 27 ዓመት ዕድሜ ክልል ዉስጥ ያሉ አራት ሴቶችን ወደ ፒኝውዶ ከተማ በመጓዝ ላይ እያሉ ተኩስ በመክፈት አፍኖ እንደወሰዳቸዉ የገለፁት ኮሚሽነሩ አስቀድሞ በአከባቢዉ የነበሩ የጎግ ወረዳ ፖሊስ አባላትና ሚሊሻዎችን በኋላም የፌዴራል ፖሊስ፣ የሀገር መከላከያ ሰራዊት እና የፀጥታ መዋቅር የጋራ ግብረ ሃይል ታፍነዉ የተወሰዱትን ለማስመለስ ቡድኑን እየተከታተሉ መሆናቸዉንም አስታዉቀዋል።በደቡብ ሱዳን የሚንቀሳቀሰው የሙርሌ ታጣቂ ቡድን ከጋምቤላ ክልል የተለያዩ አከባቢዎች በተደጋጋሚ ሰዎችን እያፈነ እንደሚወስድ የተናገሩት ኮሚሽነር ኦጉሉ በፀጥታ ሃይሎች ኦፕሬሽን ከተመለሱት በስተቀር አብዛኞቹን እንደሚገድልና ሱዳን ወስዶ ለጉልበት ስራ እንደሚሸጣቸዉም መረጃዎች እንደሚደርሷቸዉ ገልፀዋል።ኮሚሽነሩ አክለዉም በ2017 ዓ/ም ብቻ 16 ሕፃናት እና በመቶዎች የሚቆጠሩ ከብቶች በነዚህ የታጠቁ ቡድኖች ተዘርፈዋል ሲሉ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።
EthioNews #Ethiopia