
ኢትዮጵያ 350 ሚሊየን ዶላር ልትበደር ነው።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እና በዓለም አቀፍ የልማት ማህበር መካከል ለሁለተኛው ዘላቂና ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ልማት ፖሊሲ ማስፈጸሚያ የተደረገውን የብድር ስምምነት አዋጅ መርምሮ በሙሉ ድምጽ አጸደቀ፡፡
6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 2ኛ ልዩ ስብሰባውን አድርጓል፡፡
በዚሁ ወቅት የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ በሰጡት ማብራሪያ፤ 350 ሚሊየን ዶላር የብድር ስምምነቱ ከወለድ ነፃ የሆነ በረዥም ጊዜ የሚከፈል ብድር ነው።
የኢትዮጵያ መንግስት ልማት ላይ ትኩረት አድርጎ የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ላይ የሚታይ ለውጥ ማምጣቱን ተከትሎ የመጣ የብድር ስምምነት ነው ብለዋል፡፡
አጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያን ለማጠናከር እና ለማስፈፀም ታሳቢ ተደርጎ የተዘጋጀ እንደሆነም ተመላክቷል።